Fana: At a Speed of Life!

ኮሚቴው ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ጥናት እንዲደረግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች ላይ ጥናት እንዲደረግ አሳሰበ፡፡
 
ቋሚ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት የሰላም ሚኒስቴርን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
 
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ሰላም ሚኒስቴር ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የነበሩ ግጭቶች ምንጮቻቸውን እና የአፈታት ሥርዓታቸውን በማጥናት ላይ ትኩረቱን ማሳረፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ የተለያዩ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች መኖራቸውን ጠቁመው ÷ የግጭት አፈታቶቹ ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል በሚለው ላይም ጥናት ሊካሄድ ይገባል ብለዋል፡፡
 
ተቋሙ በዘመናዊ አደረጃጀት ተልዕኮውን ለመፈጸም በሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ የተረዳ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው÷ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የመከታተያ ዘዴ በቴክኖሎጂ መደገፉ የሚበረታታ መሆኑን አንስቷል፡፡
 
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው÷በተቋሙ አዲስ የተሠራው አደረጃጀት ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከል የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ ታዬ÷በግጭት አፈታት ዙሪያ ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.