Fana: At a Speed of Life!

ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል የእንስሳት መኖ እያከፋፈለ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኩምቢ ለሚገኙ 5 ሺህ አባወራዎች የእንስሳት መኖ እያከፋፈለ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ስርጭቱ በአካባቢው ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ሲሆን÷ በዚህ ዘመቻ እስከ 150 ሺህ እንስሳት ይመገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ በተለይም ቆላማ በሆኑ በቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅና ምእራብ ሐረርጌ አካባቢዎች ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ችግር ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡
ይህን ለመቅረፍም መንግሥት የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ እንዲሁም በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እያከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።
በኦሮሚያ ክልል በደረሰው ድርቅ ሳቢያ ከ14 ሚሊየን በላይ እንስሳት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የቁም እንስሳት ሕይወታቸው ሲያልፍ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በመኖ እጥረት የተነሳ በመዳከማቸው በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.