Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን በምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ የአውሮፓ ህብረት የሆራይዘን ፈንድ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ህብረቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን በምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ የአውሮፓ ህብረት የሆራይዘን ፈንድ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ።

በአውሮፓ እና በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ጠንካራ የምርምር ትብብር ለመጀመር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ምክክር እየተደረገ ነው።

በመድረኩ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት ተካሂዷል።

በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ÷ ረጅም ጊዜ የቆየውን የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በምርምርና በኢኖቬሽን ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ቀዳሚ ምርጫ መሆኗን ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ሰለሞን ቢሆን በበኩላቸው÷ ተመራማሪዎች መንግስት የሚመድበውን በጀት ብቻ መጠበቅ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ የምርምር ድጋፎችን ማሸነፍና ማምጣት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ምክክሩ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ልዑካን ጽሕፈት ቤት በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን እቅድ ለማስተዋወቅ፣ ከአውሮፓ ህብረት የሆራይዘን የምርምር አሸናፊዎችን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈልና እድሉን ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.