Fana: At a Speed of Life!

ሠላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለመ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሠላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለመ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ “የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልዕግና” በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረክ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ግርማ የሽጥላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከክልሉ ዞኖች ጥሪ የተደረገላቸው የየአካባቢው ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው።

በክልሉ የህግ የበላይነት በመፈታተን የዜጎች ሠላማዊ ኑሮ በማወክና በተዛቡ መረጃዎች ክልሉን መከፋፈል ብሎም ማፍረስ ከሚፈልጉ ሀይሎች ለመታደግ ግልፅ ውይይቶች ማድረግ፣ አንድነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን ለመስራት ያለመ መሆኑን ርዕሠ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገልፀዋል።

በህዝብ ዘንድ መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ ህግ እንዲያስከብር፣ ፍትህ እንዲያረጋግጥ የሚጠየቀውን ያህል መንግስት አጥፊዎችን ሲይዝ የተቃውሞ ድምፆች መበርታት የሚቃረኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።

ህዝብ እና መንግስት በቅርበት በመስራት፣ ህዝብ የፀጥታ መዋቅሩን በባለቤትነት እንዲቀበለው በማድረግ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ እንዲጠናከር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ከደረሠበት ጉዳት ተሻግሮ የነገም ሆነ ዛሬ ክልሉን የሚገጥሙ ችግሮችን ለመሻገር በቅርበት መስራት ወሳኝ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ዕድሎች፣ የተጋረጡ ፈተናዎች እና መውጫ መንገዶችን አስመልክቶ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ግምገማዊ መነሻ ሀሳብ አቅርበው ውይይት እየተካሄደ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.