ከፍተኛ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ ለገቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 4፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2013 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለገቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ በመዲናዋ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ ነው።
በተጨማሪም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የሚጠቀሙበት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ÷ተማሪዎቹ ውጤታማ ሆነው ከዩኒቨርሲቲ እስከሚወጡ ድረስ ቢሮው ድጋፉን እንደሚቀጥል ታውቋል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣው ተማሪዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ተማሪዎች መሸለምና መደገፍ ሞራላቸውን ለመገንባትና ለሌሎች ተማሪዎችም አርአያ እንዲሆኑ ያደርጋልም ነው ያሉት።
ተሸላሚ ተማሪዎች በበኩላቸው ድጋፉ የበለጠ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስችላቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡