Fana: At a Speed of Life!

በፍሎሪዳ ምንም የማብረር ልምድ የሌለው መንገደኛ በህመም ከወደቀው ፓይለት አውሮፕላኑን ተረክቦ በሰላም ማሳረፍ ቻለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የበረራ ልምድ የሌለው መንገደኛ አውሮፕላኑን በአሜሪካ ፍሎሪዳ አውሮፕላን ማረፊያ አሳረፈ፡፡

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ሮበርት ሞርጋን ግለሰቡ ከሚያበረው አውሮፕላን መልዕክት ሰማ ከበሃማስ በኩል፡፡

“አውሮፕላኑን እንዴት እንደማበር ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም” የሚለው የአብራሪነት ልምድ ያልነበረው የአውሮፕላኑ ተጓዥ አውሮፕላኑ ውስጥ እንደማንኛውም ተጓዥ በሰላም እየተጓዘ ነበር ይህ ክስተት እስከሚፈጠር፡፡

ሁኔታው ያልተለመደና አስደንጋጭ ቢሆንም የህይወት ጉዳይ ነውና ፓይለቱ ያጋጠመው የጤና እክል በአብራሪነት የሚያስቀጥለው ባለመሆኑ የአብራሪነት ልምድ ያልነበረው ተጓዥ አብራሪ ሊሆን ግድ ሆነ፡፡

አውሮፕላኑን እንዴት መቆጣጠርና አደጋ ሳይደርስ ማሳረፍ እንደሚችል ምንም የማያውቀው ተሳፋሪ ወደአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጥሪ አደረገ፡፡

ባደረገው የእገዛ እፈልጋለሁ ጥሪውም ሁኔታውን ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አስረዳ፡፡

በወቅቱ በቦታው ያልነበረው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ሞርጋን ከባልደረቦቹ መልዕክት ደረሰው፡፡

“ፓይለቱ አውሮፕላኑን የማብረር አቅም የለውም … ተሳፋሪዎች አውሮፕላኑን እያበረሩ ነው… ምንም የማብረር ልምድ የላቸውም” ሲል ባልደረባው እንደነገረው ይገልጻል የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ሞርጋን፡፡

ልምድ የሌለው ተጓዥ አብራሪው በወቅቱ የተረጋጋ እንደነበር ገልጾ ፥ “አውሮፕላኑን እንዴት እንደማበረው አላውቅም … እንዴት ማሳረፍ እንዳለብኝም አላውቅም” ሲልም ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ይነግረዋል፡፡

ሞርጋን ይህን ተከትሎም ልምድ የሌለው መንገደኛ አብራሪውን ደረጃ በደረጃ ይነግረው ጀመር ምን ማድረግ እንዳለበት።

ሞርጋን አውሮፕላኑን በአካባቢው ወደሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ለመምራት ቁልፍ ውሳኔ ላይ ደረሰ ፤ ውሳኔው የግድ በመሆኑ ተሳፋሪው የአውሮፕላን አብራሪ በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው እገዛ ወደታቀደለት አካባቢ መገስገስ ጀመረ።

በመጨረሻም አውሮፕላኑ ምድር ነካ ፤ ይህን በረራም ሞርጋን ልምድ የሌለው አውሮፕላን አብራሪው አውሮፕላኑን ያሳረፈበት መንገድ ፍጹም ስኬታማ ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል፡፡

ሞርጋን አክሎም ይህ በመሳካቱ እና ማንም ሰው ስላልተጎዳ በጣም ደስተኛ ነኝ ሲልም ስሜቱን ለሲ ኤን ኤን አጋርቷል፡፡

ፓይለቱ የጤና ችግር ገጥሞት እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ፥ ዝርዝር ጉዳዩን ግን ማወቅ እንዳልተቻለ ነው የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በመግለጫው የተናገረው።

ከሁነቱ በኋላ ሞርጋን አዲሱን የበረራ ተማሪውን አግኝቶ እንዳመሰገነው ገልጾ ፥ እኔ ስራዬን ነው የሰራሁት እሱ ግን ጀግና ነው ሲልም አሞግሶታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.