የሀገር ውስጥ ዜና

“የተረገሙ ጦሮች” በሚል ርዕስ ከ29 አመታት በፊት የተሰራ ፊልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለእይታ ቀረበ

By Meseret Awoke

May 12, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) “የተረገሙ ጦሮች” በሚል ርዕስ ከ29 አመታት በፊት የተሰራ እና በእርቅ እና ሰላም ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለእይታ ቀርቧል፡፡

ፊልሙ በደቡብ ክልል የኤርቦሬ ማህበረሰብ ዙሪያ የተሰራ ሲሆን፥ ፊልሙ በዶክተር አሉላ ፓንክረስት እና በሌሎችም ትብብር የተሰራ ነው፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት በሃገራችን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እምቅ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም ባህላዊውን የግጭት አፈታት ዘዴ ከዘመናዊ ህግ ጋር ተደጋግፎ ሊሰራበት እንደሚችል በማንሳት፥ ይህም ለእርቅ እና ሰላም መንገዶቻችን ብዙ ያተርፉልናል ነው ያሉት፡፡

ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በቀላል ወጪ የሚፈፀም መሆኑ፣ ቀደምት እና ቅቡልነት ያለው መሆኑ እንዲሁም አሳታፊ እና ህዝብ የኖረበት አሰራር መሆኑ ተመራጭ የግጭት አፈታት ዘዴ እንዲሆን እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡

ፊልሙ አሁን ሃገራችን ለምትገኝበት ሁኔታ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ የተናገሩት ሚኒስትሯ፥ የተጀመረውን ሃገራዊ ምክክር ውጤታማ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

ፊልሙ ዳግም ለእይታ የበቃው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር እና በተቋሙ ወዳጆች ማህበር መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በለይኩን አለም