Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በበልግ እርሻ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 4 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል እየተካሄደ ባለው የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለጹት፥ በዘር የተሸፈነው መሬት በክልሉ በ2014/2015 ምርት ዘመን በተለያየ ሰብል ለማልማት ከታቀደው 1 ሚሊየን ሄክታር ውስጥ ነው።

የዘንድሮ በልግ ዘናብ ዘግይቶ በመግባቱና የዝናብ መቆራረጥ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት በአብዛኞቹ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የበልግ እርሻው ዘግይቶ መጀመሩን ተናግረዋል።

የዝናብ ሥርጭቱ መሻሻል እያሳየ ከመጣ ማሳ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ የበልግ ልማቱን ዕቅድ ለማሳካት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው።

በበልግ ወቅት ከሚለመው መሬት 85 ሚሊየን ኩንታል የአገዳ፣ የጥራ ጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም የስራ ስር ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.