Fana: At a Speed of Life!

የዘንድሮው የአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው የአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለዘላቂ አብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በመጪው የክረምት ወራት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር 570 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማቀዱን ገልጿል ፡፡

መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አቶ አስፋው ተክሌ እንደተናገሩት ፥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ሰው ተኮር ተግባራቶችን በልዩ ሁኔታ ለመምራት እንዲያስችል ተደርጎ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሰባት ዋና ዋና ተግባራትና በ14 ንዑሳን ተግባራት ተከፋፍሎ እንደሚከናወን የተገለፀ ሲሆን ፥ ለ3ሺህ 400 አረጋውያን ፣ አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች ፣ የሀገር ባለውለታዎችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተስብ ክፍሎች በመለየት የቤት እድሳት ለማከናወን ታቅዷል፡፡

በተጨማሪም መጪውን አዲስ ዓመት፣ የመስቀል በዓል ፣ ዓረፋና ኢሬቻ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለ294ሺህ 800 ድጋፍ ለሚሹ የህበረተሰብ ክፍሎች በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነት የማዕድ ማጋራት ስራ ይከናወናል ተብሏል፡፡

በአርንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ሚሊየን የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የአካባቢ ጽዳትን ጨምሮ በአብርሆትና ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች መፅሃፍ ልገሳ፣ የፀረ ሱስ ለ20 ሺህ ዜጎች ነፃ ህክምና እና ድንበር የለሽ የበጎ ፍቃድ ተግባራት እንዲሁም ሌሎች የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች መካተታቸውን ገልፀዋል፡፡

በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1ነጥብ 5ሚሊየን በጎ ፈቃደኞችን በታቀዱ ተግባራት ሁሉ ላይ በማሳተፍ የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠንና የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዚህ የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር 570ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም 2 ነጥብ7 ቢሊየን ብር የመንግስት ወጪን ለማዳን ከተማ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ከከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.