Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በሀይል እጥረት ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ያልገቡ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀይል መቆራረጥ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ያልገቡ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞንን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ከጦርነት መልስ ወደ ኢንቨስትመንት ለመመስ ያለመ ውይይት በፍኖተ ሰላም ከተማ ተካሂዷል።

በአከባቢው መዋዕለ ንዋያቸዉን እያፈሰሱ ያሉ ባለሀብቶች በተሳፉበት ውይይት÷ ዞኑ ለምን የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማስተናገድ አልቻለም በሚለዉ ጉዳይ ላይ እና ባለሀብቶች በስራ ክንውናቸዉ የሚገጥሟቸዉን እንቅፋቶች በሚመለከት ነው ውይይት የተካሄደው፡፡

በባለሀብቶቹ የተነሱ የመሰረተ ልማት፣ የፀጥታ እና የፈጣን አገልግሎት ጥያቄዎችን ለመፍታት ዞኑ እንደሚሰራ የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ፥ ከዞኑ አቅም በላይ የሆኑ እንደ ሀይል አቅርቦት ያሉ ጥያቄዎች ከክልሉ ድጋፍ እንደሚስፈልገው ገልፀዋል።

የአማራ ክልል የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፥ በክልሉ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች በሀይል አቅርቦት ምክንያት በሙሉ አቅማቸዉ እየሰሩ እንዳልሆን አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት እስከ ሰኔ 30 ድረስ የጊዜ ቀነ ገደብ አውጥቶ፣ የማሽን ተከላ የፈፀሙ ማምረቻዎች ስራ ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ምንጃርን ምሳሌ ያደረጉት ሀላፊው÷ በአከባቢው ያለን የሀይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት በ52 ሚሊየን ብር እየተሰራ እንደሆነ እና በደብረ ብርሃንም ተመሳሳይ ስራዎች አሉ ብለዋል።

በክልሉ ያሉ ፓርኮችን የሀይል እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሰብስቴሽን የሚቋቋም መሆኑንም ተናግረዋል።

ከ1 ሺህ በላይ የተለያዩ ፋብሪካዎች ያሉት የምዕራብ ጎጃም ዞን፥ የሀይል አቅርቦት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.