Fana: At a Speed of Life!

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች – በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳዳር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ እና በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ ሰራተኞች የትውውቅ መድረክ በመፍጠር በሁለቱም አገራት የሚከናወኑ ስራዎች በተሳለጠ መልኩ ማስኬድ የሚያስችል ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን አላማ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፥ የውስጥ ጉዳዮቻችንን ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሄድ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንና እና የፌደራል መንግስቱ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አብራርተውላቸዋል።

አምባሰደሩ አክለውም ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልፀው ፥ በታላቁ የህዳሴ ግድብና በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ዙሪያ በማብራራት ኢትዮጵያ ጉዳዩ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብላ እንደምታምን ገልፀውላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳዳር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው ፥ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንደሚረዱና አገራቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን ዓቀፍ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ፥ ከንግድና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በማንሳት የትውውቅ ሰብሰባው በእንጥልጥል ላይ ያሉ ጉዳዮችን በጋራ ለማየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ ጠቃሚ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.