Fana: At a Speed of Life!

አበሽጌ ወረዳ ለብዙ አመታት የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወርዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በመዘዋወር 15 በተለያዩ ካባድ ወንጀሎችን ሲፈጽም የቆየው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

የጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው እለት በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ይፍሩ ካሳዬ (ጥበቡ ነጋሽ) ነዋሪነቱ አበሽጌ ወረዳ ሲሆን በተለያዩ ቀበሌና የሀገሪቱ ከተሞች ራሱን ሰውሮ በመዘዋወር ከባድ ወንጀል መፈጸሙ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ይፍሩ ካሳዬ (ጥበቡ ነጋሽ) አራት ሰዎች ላይ ከባድና አሰቃቂ ግድያ፣አምስት ሰዎች ላይ የከባድ ግድያ ሙከራ ወንጀል፣ ሶስት ከባድ የውንብድና ወንጀል፣ ህግ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ዘረፋ፣ የግብርና ምርቶችን በእሳት የማቃጠልና መሰል ወንጀሎችን መፈጸሙን በሰውና በሰነድ ማስረጃ የዞኑ ፍርድ ቤት አረጋግጧል፡፡

ተከሳሹ በ1997 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 (1)(ሀ) በመተላለፍ በፈጸመው ከባድ ሰው የመግደል ወንጀል እንዲሁም የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(2) እና 539 (1)(ሀ) የተደነገገውን ከባድ የሰው መግደል ሙከራ በመተላለፍ ከባድ የውንብድና ወንጀል በመፈፀሙ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

በመሆኑም የጉራጌ ዞን ወልቂጤ አከባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግንቦት 04/09/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

2ተኛ ተከሳሽ መኮንን ብቁነህ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፥ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በተሽከርካሪ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ በጸጥታ ክትትል እና ጥቆማ የተያዙ በመሆኑ በፈጸሙት የህግ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ተባባሪነት ክስ ተመስርቶበት ቆይቷል፡፡

የጉራጌ ዞን ወልቂጤ አከባቢ ከፈተኛ ፍርድ ቤት በግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት 2ኛ ተከሳሽ መኮንን ብቁነህ ላይ 3 ዓመት ከ5 ወር የእስር ቅጣትና 7 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል መወሰኑን ከጉራጌ ዞን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.