ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአጎዋ ምክንያት ምርቱን ያቆመ አምራች ኩባንያ አለመኖሩ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 4፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአጎዋ ምክንያት ምርቱን ያቆመ አምራች ኩባንያ አለመኖሩን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ÷ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያስመዘገባቸውን ዋና ዋና ስኬቶች፣ የነበሩ ተግዳሮቶችና ወደፊት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ሳንዶካን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአጎዋ ምክንያት የተለያዩ ችግሮች ገጥመው የነበረ ቢሆንም ምርቱን ያቋረጠ አምራች ኩባንያ ግን አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ 7 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚገመት ምርት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲመረት ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የተኪ ምርቶችን በተመለከተ 122 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና ለመቀነስ ታቅዶ ከ113 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ማቅረብ መቻሉንም አሳውቀዋል፡፡
አክለውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ44 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ 791 ሚሊየን ብር ከሼድ ኪራይ፣ ከለማ መሬትና በፓርኮች ውስጥ ከሚያቀርባቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ገቢ ማግኘቱን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከነበረበት እዳ በመውጣት፣ አሰራሮችን በማዘመንና በማሻሻል እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪን በመቀነስ በ9 ወራት ውስጥ 79 ሚሊየን ብር ትርፍ ማግኘት ችሏል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሀገሪቱ ውስጥ በነበረው ጦርነት ምክንያት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ተቀዛቅዘው መቆየታቸውን ያወሱት አቶ ሳንዶካን በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየመጡና በተለያዩ ሁኔታዎች እየተስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና የተመዘገቡ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት፣ የካሳና የድንበር ጉዳይ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር የሚገናኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የተካሄደው የህልውና ጦርነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈተና ሆነው መቆየታቸውን አሳውቀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የለውጥ ሪፎርሞችን እያከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቁመው ይህንንም ተግባራዊ በማድረግ በቀጣይ የተሻለ ተቋማዊ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እደሚሰራ ማረጋገጣቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል፡፡