በፕሪሚየር ሊጉ መከላከያ እና ፋሲል ከነማ ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በ23ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መከላከያ ሲዳማ ቡናን 5 ለ 3 አሸንፏል፡፡
ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት በተካሄደው እና ስምንት ጎሎችን ባስተናገደው ጨዋታ መከላከያ ከባህርዳር ስታዲየም ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል፡፡
ለመከላከያ ተሾመ በላቸው ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር፥ ቢኒያም በላይ፣ አዲሱ ቱሳ እና ክሌመንት ቦዩ ቀሪ ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡
ለሲዳማ ቡና አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ዳዊት ተፈራ ቀሪዋን አንድ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡
መከላከያ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 30 በማደረስ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በሌላ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
አመሻሽ ላይ በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ለፋሲል ከነማ የማሸነፊያዋን ጎል ፍቃዱ አለሙ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።