የዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት የኢትዮጵያ ወኪል ቶም ጋርድነር የስራ ፈቃድ ተሰረዘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት የኢትዮጵያ ወኪል ጋዜጠኛ ቶም ጋርድነር በሀገሪቱ መስራት የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ መሰረዙን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ለዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጠኛ በጻፈው ደብዳቤ ነው በኢትዮጵያ መስራት የሚያስችለውን ፍቃድ መሰረዙን ያስታወቀው፡፡
ባለስልጣኑ በደብዳቤው እንዳመላከተው ጋዜጠኛው ሙያውን እና የኢትዮጵያን ህግና ደንብ ባከበረ መልኩ ባለመስራቱ ፍቃዱን መሰረዙን ነው የገለጸው፡፡
ባለስልጣኑ ከአሁን በፊት ለጋዜጠኛው ተደጋጋሚ የጽሁፍና የቃል ማስጠንቀቂያዎች እንደሰጠውም ነው የተነሳው በደብዳቤው፡፡
ሆኖም የዘ ኢኮኖሚስቱ ዘጋቢ ቶም ጋርድነር ሙያውን እና የኢትዮጵያን ህግ እና ደንብ አክብሮ ሊሰራ ባለመቻሉ የስራ ፈቃዱን ሰርዣለሁ ሲል ነው ባለስልጣኑ በደብዳቤው የገለጸው፡፡
ባለስልጣኑ አክሎም ዘ ኪኮኖሚስት በቶም ጋርድነር የሚተካ የሙያውን ሥነ ምግባር በማክበር ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ ጋዜጠኛ እንዲመድብ አሳስቧል፡፡