Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የቆላማ አከባቢ አርብቶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል እየተተገበረ ያለው ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆላማ አከባቢ አርብቶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል በአለም ባንክ ድጋፍ እየተተገበረ ያለው ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶ አደር ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የአርብቶ አደር የአኗኗር ጥናት ዳይሬክተር አቶ ከተማ ኡርጋ በቆላማ አከባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ18 በላይ ወረዳዎች መካተታቸውን ጠቁመው፥ በመኖ ልማት ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣትን ትኩረቱ አድርጎ በሚሰራው ፕሮጀክት የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ በተሰጠው የመኖ ልማት በቦረና ዞን ለውየ ወረዳ ብቻ ከ217 ሄክታር በላይ መኖ ማልማት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖችን የያዘው የጭሮ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ወርቁ ጋዲሳ÷ በሁለቱ ዞኖች ሶስት ወረዳዎች እና 18 ቀበሌዎችን በፕሮጀክቱ በማቀፍ ከ70 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፥ ከዚህ ውስጥም ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአርብቶ አደሩ አከባቢዎች ላይ ያለውን መልክአ ምድር እንዲያገግም መስራት፣ ለስራ አጡ የስራ እድል መፍጠር፣ የአርብቶ አደሩን ኑሮ እንዲሻሻል ማድረግ፣ የከብት መኖ አቅርቦት በራሱ አርብቶ አደሩ ማልማት እንዲችል ማድረግ፣ ዝቅተኛ የመስኖ ልማቶችን እንዲያከናውኑ እና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ መሰረተ ልማቶችን መገንባት የፕሮጀክቱ ዓላማዎች መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ወዲህ በቆላማ አከባቢዎች ያሉ አርብቶ አደሮች ላይ የትምህርት ተቋማትን መገንባትና የማስፋፊያ ስራዎችን ጨምሮ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውም ተገልጿል፡፡
ከሶማሊያ እና ከፑንት ላንድ የመጡ ልዑካንም÷ በአለም ባንክ የሚደገፈውን የቆላማ አከባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አፈጻጸም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ የልምድ ልውውጥና ጉብኝት እያደረጉበት ነው።
በይስማው አደራው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.