Fana: At a Speed of Life!

ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ኃይል በኡጋንዳ ለመንቀሳቀስ ፈፅሞ አይፈቀድለትም – የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ኃይል በኡጋንዳ ለመንቀሳቀስ ፈፅሞ እንደማይፈቅድለት የኡጋንዳ የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ኢታማጆር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርኃኑ ጁላ ከኡጋንዳ የመከላከያ ሚኒስትር ቪንሴንት ሲሴምፒጃ ጋር በወቅታዊ የሁለቱ አገሮች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱ የሁለቱ አገራት የመከላከያ ዘርፍ ስምምነት ያለበትን ደረጃ የዳሰሰ ሲሆን፥ በቀጣይ ስምምነቱን ለማደስም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህም ሥምምነቱን የማደስ ሥራ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዲፈፀም መመሪያ ተሰጥተዋል፡፡

ሁለቱ ባለስልጣናት በዋናነት ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘገብ ስለነበረውና አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን በአሜሪካ፣ በግብጽና በደቡብ ሱዳን በመታገዝ በኡጋንዳ አማካኝነት እገዛ እያገኘ ነው የሚለውን አሉባልታ ሚኒስትሩ ፈፅሞ ከዕውነት የራቀ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ኢትዮጵያን የአፍሪካ እናት አድርጋ እንደምትመለከታትና ማንኛውም ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ኃይል በኡጋንዳ ለመንቀሳቀስ ፈፅሞ እንደማይፈቀድለት አረጋግጠዋል።

አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያና በኡጋንዳ መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ የጠበቀ ግንኙነት ለማደፍረስ እየሰሩ በመሆኑ ከእነዚህ አፍራሽ ኃይሎች መጠንቀቅ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.