Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል – በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔት ዌበር ተናገሩ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ እና የልዑካን ቡድን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እና አጋርነት መኖሩን ገልጸው÷ የነበረው ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለልዑኩ ባደረጉት ገለጻ፥ ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ምክክር ለማድረግ እየተሰናዳች መሆኑን እና ምክክሩ በአገራችን የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

አክለውም ለትግራይ ክልል የሚደረገውን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በሙሉ አቅሙ ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየና በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስረዳታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔት ዌበር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ያላቸው መልካም ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል ያለው ግጭትም ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ በኢትዮጵያ ሠላም እንዲሰፍን ከምንጊዜውም በላይ የአውሮፓ ህብረት ፍላጎት እንዳለው እና ለዚህም የሰላም አማራጭ እንዲሳካ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.