Fana: At a Speed of Life!

ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ እና ጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ሁሉ የፀጥታ መዋቅሩ እና ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ይሁን – የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ ለጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ሁሉ የፀጥታ መዋቅሩ እና ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆን የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ ለጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ሁሉ የፀጥታ መዋቅሩ እና ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆን የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በዝርዝር ገምግሟል፡፡ የወያኔ ወራሪ ቡድን በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እያነሳሳ በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል፡፡ ይህን አደገኛ ቅዠቱን ለመመከትና ለመቀልበስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት በአንክሮ ተወያይቶበታል፡፡ የጸጥታ ምክር ቤቱ በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ መሆን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በሌላ በኩል በየደረጃው በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ጎልተው ከወጡ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሕግ ማስከበር ሥራ መላላት ተጠቃሽ መሆኑን የጸጥታ ምክር ቤቱ በጥልቀት አንስቷል፡፡
በቅርብ ጊዜ ደግሞ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአማራን የውስጥ አንድነት ለማዳከም፣ ሕዝብ ከሕዝብ በማጋጨትና በማጋደል ላይ ተሰማርተው ለጠላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሠሩ ያሉ የተደራጁና ያልተደራጁ ኃይሎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ተጨባጭ የፀጥታ ስጋት እየፈጠሩ መሆኑን በዝርዝር ተወያይቶበታል፡፡
እነዚህ ኃይሎች በእምነት፣ በፖለቲካ፣ በብሔር ሕዝባችን እየከፋፈሉ የአማራን የውስጥ አንድነት በማዳከም ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርጉት ሙከራ በአጭር ካልተቀጨ በሕዝባችንና በክልላችን ሰላምና ደኅንነት ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
የሕገ-ወጥ ንግድን በማስፋፋት ካለው ሀገራዊ የምርት እጥረት በተጨማሪ ሰው ሠራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ፣ ምርትን ለጠላት በኮንትሮባንድ አሳልፈው የሚልኩ፣ የሕዝብን ሃብት የሚዘርፉ፣ የዜጎችን ነጻ እንቅስቃሴ የሚገድቡ ድርጊቶች በየአካባቢው እያቆጠቆጡ መጥተው ለክልሉ የፀጥታ ስጋት መሆናቸውን ጸጥታ ምክርቤቱ ለይቷል፡፡ ከዚህም በላይ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ስጋት ውስጥ እየጣለ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም መሳሪያን ለመሞከር በሚል በሐዘንና በደስታ ላይ በግዴለሽነት በሚተኮስ ጥይት የንጹሐንን ህይወት እየቀጨ እና የሕዝባችን የፀጥታ ስጋትና የሐዘን ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ጸጥታ ምክር ቤቱ በአንክሮ ተመልክቷል፡፡
ሕገ-ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት ሥር እየሰደደ በመምጣቱ ሕገ-ወጥ ታጣቂዎች በሚያደርጉት ያልተገባ እንቅስቃሴ የክልሉን ልማቶች እያዳከመ፤ የዜጎችን ነጻ እንቅስቃሴ እየገደበ ፤ የኢንቨስትመንት እድሎችን እየዘጋ፣ የተፈጠረውን የሥራ ዕድል እያጠፋ፣ ለቀጣይ ልማትም እንቅፋት በመሆንና በአጠቃላይ የአማራን ክልል ልማት በአደገኛ ሁኔታ እየተፈታተነ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥቶ ተመልክቷል፡፡
እነዚህ ሕገ-ወጥ ተግባራት በከተማም ሆነ በገጠር በአጭር ጊዜ ማረም ካልተቻለ የአማራ ክልል ልማት የሚያስቀጥል ሳይሆን የነበረውንም የሚያመክን የሕገ-ወጥነትና የሥርዓት አልበኝነት መናኸሪያ የሚያደርግ መሆኑን በመረዳት ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል መልክ መያዝ እንዳለባቸው ታምኖበታል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ ወገኖቻችንም በአግባቡ ምግብ እንዲያገኙ አድርጎ ወደ ቀያቸው ጊዜ መመለስ ካልተቻለ የፀጥታና ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ፀጥታ ምክር ቤቱ ተወያይቶበታል፡፡
ከዚህ አንጻር መንግሥት በየደረጃው ሕግ የማስከበር ሥራውን በጥብቅ በመፈጸም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር አለበት በማለት ሕዝቡ በተለያዩ መድረኮች ያነሳቸውን ጥያቄዎች መርምሮ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
ስለሆነም የክልሉ ጸጥታ ምክር ቤት የአማራ ክልል ያለበትን የፀጥታ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የወያኔን ዳግም ወረራ ለመቀልበስና ለመከላከል የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ሰላምና ደኅንነትን መጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል። ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ ለጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ሁሉ የፀጥታ መዋቅሩ፣ ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በመሆኑም በአንድ በኩል ከፌደራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ከወያኔ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅና በዝግጁነት መቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጣችን ለወያኔ ሴራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩትን ሕገ-ወጦችንና ሥርዓት አልበኞችን በመቆጣጠር የክልላችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ግንባር ቀደም የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆኑ ወስኗል፡፡
ስለሆነም የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት በየደረጃው የጸጥታ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ሕገወጥነትን ለመቆጣጠርና ሕግን ለማስከበር ተገቢ ነው ያላቸውን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በመሆኑም የክልላችን ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች ሰላምና ደኅንነታችን ለመጠበቅ እና የውስጥ አንድነታችን ለማጠናከር የፀጥታ መዋቅሩ በሚወስደው እርምጃ ሁሉ ተባባሪ እንድትሆኑ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት
ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም
ባሕር ዳር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.