በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወታደራዊ መንግስቱን በመቃወም ሰልፍ ወጡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን ወታደራዊ መንግስት በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በትናንትናው እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ እና በፖለቲካ ተቀናቃኞች መካከል ሊያደርገው ያቀደውን ድርድር አንቀበልም በማለት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሀገሪቱ ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ማፈላለግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በያዝነው ሳምንት ከሱዳን የፖለቲካ ተቀናቃኞች ጋር የሶስትዮሽ ውይይት ሊያደርግ ነው መባሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ መፈክሮችን በማሰማት እና በሀገሪቱ የሲቪል አገዛዝ እንዲኖር የሚጠይቅ ድምጽ በማሰማት ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት አምርተዋል ነው የተባለው።
በተቃውሞ ሰልፉ ከወታደራዊ አገዛዙ ጋር ምንም አይነት ድርድር፣ሽርክና እና ስምምነት የለንም የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል ተብሏል።
የመጀመሪያው ዙር የሶስትዮሽ ውይይቱ በግልጽ የሚደረግ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን ህዝቡ መረጃ የሚያገኝበት መንገድ ይመቻቻል መባሉን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የሱዳን ባለሙያዎች ማኅበር (ኤስ ፒ ኤ)፣ የጁባውን የሰላም ስምምነት ያልተፈራረሙ የሱዳን አማፂያን እና የኮሚዩኒስት ፓርቲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርድርን በመቃወም ተሳትፎ ላለማድረግ የወሰኑ ሲሆን የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች ጥምረት የተባለው ፓርቲ በውይይቱ ለመሳተፍ መስማማቱ ተገልጿል፡፡