Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ እና አፋር ክልሎች አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውሳኔ አሳለፉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ እና አፋር ክልሎች በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውሳኔ አሳለፉ፡፡

ውይይቱ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፣ የሶማሌ እና አፋር ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን÷ በሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች መካከል አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነው ተወያይተው ውሳኔ ያሳለፉት፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የረጅምና የአጭር ጊዜ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት የተካሄደ ሲሆን÷ በውይይቱ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት በግጭት አከባቢዎች ያሉ የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ሀይሎችን ማንሳትና ከግጭት የጸዳ አካባቢ መፍጠር፣ ግጭቶችን የፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደርጉ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ስለሚኖሩ ለመፍትሄው ተከታታይ የህዝብ መድረክ ማዘጋጀትና ውጤቱን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ተስማምተዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረው አለመግባባት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለስና ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ መስራት ከስምምነት የተደርሱ ጉዳዮች ሲሆኑ፥ በዚህ አንቀጽ አፈፃፀም የፌደራል መንግስትና ሁለቱ ክልሎቹ በትብብር እንደሚሰሩ ነው የተመላከተው፡፡

በተጨማሪም የግጭቶቹን መሰረታዊ መንስኤ በጥልቀት ማጥናትና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም እንዲሁ ከስምምነት ተደርሷል።

በውይይቱ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ÷ “ውሳኔዎችን በሰለጠነ አካሄድ ተግባራዊ ካደረግን በተደጋጋሚ ግጭት በሚፈጠሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት መቀየር ይቻላል̎” ብለዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፥ የሶማሌና አፋር ህዝቦች ባህል፣ ሃይማኖት እና የስነ ምድራዊ ወሰን የሚጋሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡

በሁለቱ ህዝቦች መካከል የዘለቀውን መልካም ግንኙነት ለመመለስ ትርጉም ያለው ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ልዑኩ በደጋህሌ ቀበሌ የሚገኙ በመስኖ የለሙ የእርሻ ቦታዎችንና የእንስሳት እርባታን መጎብኘቱን ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.