Fana: At a Speed of Life!

ቆቃ በደለል ምክንያት የሚጠበቅበትን የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ አይደለም

አዲ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በደለል ምክንያት መቀነሱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አከባቢ እና አከባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያረጋገጠው ሰሞኑን በቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመስክ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ከሐይቁ ደለል የማስወገድ ሥራ ላለፉት 20 ዓመታት ያህል የተቋረጠ በመሆኑ፥ ሐይቁ ለከፍተኛ የደለል ክምችት መዳረጉን እና በዚህም የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በእጅጉ መቀነሱን ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡
የሐይቁ ጥልቀትም ከ10 ሜትር ወደ አንድ ሜትር አካባቢ መቀነሱን ከዘርፉ ባለሙያዎች ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ እንደተደረገለት አመልክቷል።
በሐይቁ የውኃ ይዘት መቀነስ ምክንያትም ከሦስቱ ተርባይኖች አንዱ ሥራ እንዳቆመ ያረጋገጠው ቋሚ ኮሚቴው፥ ባለፉትጊዜያት 42 ሜጋ ዋት ያመነጭ የነበረው ይህ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አሁን ከ10 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ኃይል እያመነጨ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ መስፍን ዳኜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚጠበቀውን ያህል ኃይል እያመነጨ አለመሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልሉ መንግስት እና በተለያዩ እርከኖች የሚገኙት አመራሮች የተቀናጀ እና የጋራ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ወልደማርያም ጥላዬ በበኩላቸው፥ ከሞጆ ቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጣው ኬሚካል ፍሳሽ ሐይቁን እንደበከለው፣ የበፈር ዞን ሕግ ባለመኖሩ ሐይቁ ከሰው እና እንሰሳ ንክኪ ነጻ አለመሆኑ እና በደለል መሞላቱ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.