Fana: At a Speed of Life!

እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ በመሆኑ በአብዛኛው የሀገሪቱ አከባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መጥቷል- መንግስት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ በመሆኑ በአብዛኛው የሀገሪቱ አከባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች፣ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና በመደበኛ የመንግስት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የሰላም እና የደህንነት ሁኔታዎችን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ ጽንፈኝነትና ፖለቲካዊ ገጽታ ባላቸው መገፋፋቶች ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት የህብረተሰቡን ደህንነት እና ሁለንተናዊ ሀገራዊ አንድነትን ለማስከበር እየተወሰደ ያለው ህብረተሰብን ያሳተፈ የተቀናጀ እርምጃ በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡
በህብረተሰብ ንቅናቄ እና ድጋፍ ታጅቦ እየተካሄደ የሚገኘው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ውጤታማ እየሆነ በመምጣቱ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እየተደረጉ ባሉ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በጎንደር በቀብር ስፍራ በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተከሰተ አለመግባባት የተፈጠረውን ግጭት ለማስፋፋት የተደረገው ሙከራ በሰላም ወዳዱ የህብረተሰብ ክፍል እና የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ርብርብ መለስተኛ ጉዳት ቢያስከትልም ሴራው ግን ከሽፏ ብለዋል ፡፡
ጥቃቱ በአንድ በኩል አብያተ ክርስቲያናትን እና የጸሎት ቤቶችን በሌላ በኩል ደግሞ መስጊዶችን ሰለባ በማድረግ የተለያየ ሀይማኖት የሚከተሉ ወንድማማች ሕዝቦችን በማጋጨት በሕዝቦች የጋራ ጥረት የቆየውን አንድነት፣ ወንድማማችነት እና አብሮነት እንዲሸረሸር በማድረግ ሀገር የማፍረስ ዓላማ ነበረው ነው ያሉት።
 
መላው ሕዝቡ አንድ ሆኖ በመቆሙ ለዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ትልቅ ቦታ በመስጠቱ የግጭቱ ፍላጎት እና ውጥን ጸረ ኢትዮጵያዊ አቋም ካላቸው አካላት እና የውስጥ ባንዳዎች ጥምረት የሚፈጸም መሆኑን ህዝቡ በመረዳቱ ሴራውን እና ድርጊቱን ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንዳከሸፈው ተናግረዋል።
 
በኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየወሰደ ያለው የተቀናጀ ዘመቻም ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያመለከቱት።
 
በአሁኑ ሰዓት ኦፕሬሽኑ በተቀናጀ መልኩ በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ፣ በሰሜን እና ምዕራብ ሸዋ ፣ በቦረና እንዲሁም በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ተጠናክሮ ቀጥለዋል፡፡
 
ዘመቻው በፀረ ሽብርና በፀረ ሽምቅ ልዩ ኮማንዶ የታገዘ በመሆኑ ከፍተኛ ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል።
 
በዮሐንስ ደርበው እና ሀብታሙ ተክለስላሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.