Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች አለመውጣቱን መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ከያዛቸው የተለያዩ አካባቢዎች አለመውጣቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች እንደወጣ ቢያወራም አሁንም በአማራ ክልል በወረራ ከያዛቸው አዲአርቃይ፣ ጸለምት፣ አበርገሌ እና ሌሎች አካባቢዎች እንዲሁም ከአፋር ክልል ደግሞ በራህሌ፣ ኮኖቫ፣ አብአላ፣ መጋሌ ወረዳዎች አልወጣም ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ የሰብዓዊ እርዳታ እና ሰሜኑን የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ÷ መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የክልሉን ነዋሪዎች ለመታደግ ሲባል የግጭት ማቆም ውሳኔን ተከትሎ በየብስ እና በአየር ትራንስፖርት የሚጓጓዘው የሰብዓዊ እርዳት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

የእርዳታ ፍሰቱንም የተሳለጠ ለማድረግ መንግስት ከእርዳታ ድርጅቶች የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን መፍታቱንም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንትም የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 165 ያህል ተሸከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸው በመግለጫው ተነስቷል፡፡

መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን የእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ማቅረብ የሚችሉትን እርዳታ እንዲያቀርቡ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም፥ በአንጻሩ የህወሃት ወራሪ ኃይል የእርዳታ ማጓጓዝ ስራው እንዳይሳለጥ እንቅፋት እየሆነ ነው ብለዋል ዶክተር ለገሰ በመግለጫቸው፡፡

የእርዳታ እህል ለማሳለጥ ሲባል ከአፋር ወጥተናል በሚል የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የሚረጩት ወሬም መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሽብርተኛው ህወሓት፥ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይቀርብ እያስተጓጎለ ነው፤ “በከበባ ውስጥ በማስገባት ትግራይን በርሃብ እየቀጣ ነው” በሚል የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት መንግስትን ሲከሱ ይደመጣል ብለዋል ዶክተር ለገሰ፡፡

ይሁን እንጂ፥ የአማራ እና የአፋር ክልል ወረዳዎችን በጉልበት ወርሮ እና ተቆጣጥሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማፈናቀል ለስቃይና እንግልት እየዳረጉ ተከበብኩ፣ ተራብኩ ወዘተ የሚለው የተለመደ ድራማ እና መዝሙር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ዶክተር ለገሰ ቱሉ አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ድርጊታቸው ሕዝብን በማዋረድ ሰግብግብ ፍላጎታቸውን በሕዝብ ሞት እና ስቃይ ለማሟላት የሚያደርጉት እኩይ ሴራ ነው ብለዋል፡፡

“ከበባውን ለማስከፈት ሲባል የግድ ወደ ጦርነት ለመግባት እገደዳለሁ” በሚል የሚገለጸው የጦርነት ጉሰማ እና ፉከራም ዳግም የትግራይን ወጣቶች ለማስጨረስ እንደሆነም በመግለጫው ተነስቷል፡፡

የአሸባሪው ቡድን ዳግም በትግራይ ወጣቶች ደም እኩይ ፍላጎቱን ለማሳካት ለመጠቀም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የትግራይ ሕዝብ እንዲታገል መንግስት ጠይቋል፡፡

 

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.