Fana: At a Speed of Life!

በየጊዜው እየተባባሰ ከመጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጭበርባሪዎች ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥምር ግብረ-ኃይሉ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በየጊዜው እየተባባሰ ከመጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጭበርባሪዎች ሰለባ ላለመሆን ዜጎች ማንነታቸው ከማይታወቁ ግለሰቦች ጋር በበይነመረብ በሚደረጉት ግንኙነት ላይ ጥንቃቄ እንዲወስዱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥምር ግብረ- ኃይል አሳሰበ።
ግብረ ኃይሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች በይዘትም ሆነ በአፈጻጸም ስልታቸው ውስብስብ እየሆኑ ከመምጣታቸው ባሻገር በርካታ ግለሰቦች የጉዳቱ ሰለባ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
የማጭበርበር ወንጀሎቹ በዋናነት የሚፈጸሙት በውጭ ሀገር የሚኖሩ፣ በቱሪስት ቪዛ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች መሆኑንም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያውያን በስፋት የሚጠቀሟቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ማለትም ፌስቡክ፣ ኢ-ሜይል፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ኢሞና ቫይበርን በመጥለፍና ወዳጅ መስሎ በመቅረብ ወንጀሎቹ እንደሚፈጸሙ ከተደረገው ክትትል ማወቅ እንደተቻለም ተገልጿል።
የማጭበርበር ተግባሩን የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ሀሰተኛ የሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ድርጅቶችን ሰነድ፣ የፋይናንስ ተቋማትና የጉምሩክ ሰነዶች የተቋም መለያዎችና ሎጎዎችን፣ የኃላፊዎችን ፊርማ፣ መታወቂያ እንዲሁም የተለያዩ ውሎችን ጭምር ለማጭበርበሪያነት እንደሚጠቀሙ አመልክቷል፡፡
የወንጀሉ ፈጻሚዎች የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በየጊዜው የሚለዋወጡ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ በውጭ አገራት በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ በማስመሰል በኢትዮጵያ ውስጥም በዚህ ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና አብሯቸው የሚሰራ ሰው እንደሚፈልጉ በመግለጽ፣ ለተማሪዎች በውጭ አገር የትምህርት ዕድል አመቻችተናል በማለትና ሌሎች ተመሳሳይ የማጭበርበሪያ መንገዶችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።
የተለያዩ የጽሕፈት መሳሪያዎችና ላፕቶፖች እንደላኩ በመግለጽ÷ ውጭ አገር ቤተሰብ ያላቸዉን ግለሰቦች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚደረግን የማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነት በመጥለፍ ቤተሰቦቻቸው ዕቃ እንደላኩላቸው በማስመሰልና በጠለፉት መስመር እንደ ቤተሰብ ሆነው በመጻፍ ማረጋገጫ በመስጠት ጭምር እንደሚያታልሉም ተመልክቷል።
በተጨማሪም በፍቅር እንደወደቁና አግብተው ወደ ዉጭ ሃገር መውሰድ እንደሚፈልጉ በማሳመን፣ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭ ሃገራት ወታደሮች ነን በማለት ከአሸባሪዎች በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር እንደያዙና ገንዘቡን ወደ ሃገራቸሀ ይዘው ለመግባት አስቸጋሪ ስለሆነ ዶላሩን ወይም የውጭ አገር ገንዘቡን በስማቸው ልከንላችኋል በማለትም በርካታ ዜጎችን እንዳጭበረበሩ ተጠቅሷል።
በሌላ መልኩም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ እንደ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እድለኛ ሆነው እንደመረጧቸው እና የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ከውጭ ሀገር ሽልማት እንደላኩላቸው በማስመሰል እና ሌሎች የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብሏል መግለጫው፡፡
ግለሰቦቹ የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን ተጠቅመው ካሳመኑ በኋላ ውድ እቃዎችን ማለትም የወርቅ ሰዓት፣ ብራስሌት፣ ሃብል፣ ሽቶ፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ስማርት ስልኮች፣ ላፕቶፕ እንዲሁም የውጭ ሀገር ገንዘብ እንደላኩ በማስመሰል እንደሚያታልሉ ተገልጿል።
ለዚህም የላኪና የተቀባይ ስም እና አድራሻ የተጻፈበትን ማሸጊያና የጉምሩክ ሂደቱን በቪዲዮ ቀርጸው በመላክ እቃውን በተጓዦች በኩል በዲፕሎማት፣ በጉምሩክ፣ በፖስታ ቤት፣ በዲኤች ኤል፣ ስካይ ወርልድ ወይም በሌሎች አማራጮች ልከንላችኋል በማለት እቃው ለተላከበት ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ሃገር ውስጥ በሚገኙት ተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ሃሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም የተከፈተ የሂሳብ ቁጥር ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ካሳመኗቸው በኋላ የገባዉን ገንዘብ ወዲያውኑ ወጪ በማድረግ ወንጀሉን ይፈጽሙታል ብሏል መግለጫው፡፡
በዚህ የማጭበርበር ድርጊቶች ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች በተጨማሪም ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ማተም፣ ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል እንዲሁም የአደንዛዥ እፅ ዝውውር ወንጀል ጭምር ላይ ተሳታፊ ሆነዉ የተገኙ ሲሆን÷ በተደረገው ክትትል የውጭ አገር ዜጎች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተጣርቶባቸዉ በማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ እና ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ላይ የሚገኙም እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
ይህ የማጭበርበር ድርጊት ግለሰቦች ለረዥም ጊዜ ያፈሩትን ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት በመሸጥ ለዚሁ ክፍያ በማዋል ከሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተጨማሪ ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው እውቅና ውጭ የጋራ ንብረትን መሸጥና በዚህ ምክንያት ለትዳር መፍረስ እና ለቤተሰብ መበተን መንስኤ በመሆን ላይ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ከፋይናንስ ተቋማትና ከግለሰቦች በአራጣ ጭምር ገንዘብ በመበደር ከፍተኛ ወለድ እንዲከፍሉ በመደረጋቸው በግለሰቦች ህይወት ላይ ጫና እንዲፈጠርና ህይወታቸው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ዜጎች በድንገት ሀብት ንብረታቸውን በማጣታቸው የጤና መታወክ ብሎም የስነ-ልቦና ችግር እንዲደርስባቸው በማድረግ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝም መግለጫው አመልክቷል፡፡
ይህን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ዜጎች የማህበራዊ ሚዲያን ሲጠቀሙ ማንነታቸው ከማይታወቁ ግለሰቦች ጋር የሚደረጉ ግንኙነትን በጥንቃቄ ማየት እንዳለባቸው ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል፡፡
በማንኛውም መንገድ እቃ ተላከላችሁ ሲባሉም እቃውን አይተው ሳያረጋግጡ ምንም አይነት ክፍያ አለመፈጸም፣ እቃው ተላከ ወደተባለበት ተቋም በአካል በመሄድ በስማቸው የተላከ እቃ ስለመኖሩ ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡
እንዲሁም በጉምሩክ፣ በፖስታ ቤት፣ በዲኤች ኤል ወይም በሌሎች ድርጅቶች በኩል የተላከ እቃ ወጪ ለማድረግ ገንዘብ ገቢ የሚደረገው በተቋማቱ ስም በተከፈተ የሂሳብ ቁጥር እንጂ በግለሰቦች ስም በተከፈተ የሂሳብ ቁጥር አለመሆኑን ማወቅና በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምንም ገንዘብ ገቢ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባ መግለጫው አስገንዝቧል።
እንዲህ ያለ ድርጊት ሲያጋጥምም በቅርብ ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ሪፖርት በማድረግ የዜግነት ግዴታን መወጣትና ራስንም ከጉዳት መከላከል እንደሚገባ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.