Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳትፎ ያልነበረቸው 7 ሺህ የሚጠጉ ንፁሃንን መግደሉን ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ ያልነበረቸው 6 ሺህ 985 ንፁሃን ዜጎችን መግደሉን ጥናት አመለከተ፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ያደረሰው ጉዳት በተመለከተ ጥናት ሲያደርግ የነበረው ቡድን የጥናቱን ጥቅል ውጤት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ጥናቱ አምስት ወራትን የወሰደ ሲሆን÷ በአስር ዩኒቨርሲቲዎች እና በብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ትብብር ሲደረግ የቆየ መሆኑ ተነግሯል።

ጥናቱ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው ነፃ የወጡ የክልሉን ስምንት ዞኖች ያካተተ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ቡድኑ በፈፀመው ወረራ ከ240 ሺህ በላይ ሰዎች የሰብዓዊ ጉዳት ሰለባ ሲሆኑ ÷ 7 ሺህ 460 ዜጎች ደግሞ በሃይል ታፍነው በመወሰዳቸው የት እንዳሉ አለመታወቁ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በጦርነቱ ሚና ሳይኖራቸው ከተገደሉት 6 ሺህ 985 ዜጎች ውስጥ 1 ሺህ 797ቱ በጅምላ ተጨፍጭፈው የተገደሉ መሆናቸው በሪፖርቱ ቀርቧል።

ቡድኑ ዘግናኝ ግድያዎችን ከመፈጸም በተጨማሪ እጅግ አስነዋሪ በሆኑ መንገዶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችንም መፈፀሙን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ ባደረሰው አስከፊ የሰብዓዊ ጉዳት የአስገድዶ መድፈር ሰለባ የሆኑት 1 ሺህ 782 ዜጎች መሆናቸውንም ጠቁሟል።

በጥናቱ 748 የጤና ተቋማት፣ 1 ሺህ 145 የትምህርት ተቋማት፣ 868 የቱሪዝም ተቋማትና መስህቦች በአሸባሪው ህወሓት የወደሙና የተዘረፉ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ፣ የጤና አገልግሎት አለመኖር፣ ዜጎች ለሞትና ለከፋ የጤና ችግር መዳረጋቸውና በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ አስከፊ ጉዳት በመድረሱ መጠነ ሰፊ ስራ አጥነት መከሰቱ ተመላክቷል፡፡
በበርናባስ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.