Fana: At a Speed of Life!

ከ131 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት 131 ሚሊየን 481 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ነው 40 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 90 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የተያዙት፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ድሬድዋ፣ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ÷በቅደም ተከተላቸው 14 ነጥብ 7 ሚሊየን፣ 9 ነጥብ 7 ሚሊየን እና 5 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸው ተገልጿል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ ነው የተያዙት፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 15 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.