በደንዲ ሀይቅ ላይ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጂ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል በሆነው የደንዲ ሃይቅ ላይ ዘመናዊ ኢኮ-ቱሪዝም ሎጂ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የደንዲ ሐይቅ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኝ ሲሆን÷ ከአዲስ አበባ 127 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የመሰረት ድንጋዩን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የጣልያኑ “ዊ ቢውልድ” ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒዬትሮ ሳሊኒ እና የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ማስቀመጣቸውን ኦቢኤን ዘግቧል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎችም ተገኝተዋል።
የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ዋና ዓላማው በቅድሚያ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቀሚነት ማረጋግጥ ነውም ተብሏል፡፡
በገበታ ለሀገር የሚለማው የወንጪ ደንዲ የተቀናጀ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም የግንባታ ስራው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጀመሩ ይታወሳል።