በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች በቲቢ በሽታ ሕይወታቸው ያልፋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች በቲቢ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ እና ከቀዳሚዎቹ አምስት ተላላፊ በሽታዎች መከላከል ቲቢ የመጀመሪያው እንደሆነ ተገለጸ።
ቲቢን በማጥፋት የድርሻችንን እናበርክት፤ ሕይወትን እንታደግ በሚል መሪ ቃል የዓለም የቲቢ ቀን በድሬዳዋ አስተዳደር የተከበረ ሲሆን÷ የቲቢ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ተጠይቋል፡፡
በዓለም ለ40ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ25 ጊዜ በተከበረው የቲቢ ቀን መርሀ ግብር ተገኝተው የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደገለጹት÷ የቲቢ በሽታ በትንፋሽ የሚተላለፍ በመሆኑ የበሽታው ምልክቶች የሚታይባቸው ህሙማን በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት እንዲሄዱና ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግ ያስፈልጋል።
በምርመራ የቲቢ በሽታ የተገኘባቸው ህሙማንም ህክምናቸውን ሳያቋርጡ መከታተልና ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው አሳሰበዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው÷ የቲቢ በሽታ የተገኘባቸውን ህሙማን ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ከማድረግ አንፃር አፈጻጸሙ 95 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ ለመለየትና ለማከም በተዘጋጀው የህክምና ማዕከል ከድሬዳዋና ከምስራቅ ኢትዮጵያ የህክምና ቅብብሎሽ በማድረግ ለ256 ታካሚዎች አገልግሎት በመስጠት 70 በመቶ ያህሉ ታካሚዎች ህክምናቸውን በስኬት አጠናቀዋል ነው ያሉት።
የቲቢ በሽታ በትንፋሽ የሚተላለፍና በኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ አምስት ተላላፊ በሽታዎች መከላከል የመጀመሪያውና ለህመምና ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ እንዲሁም በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን የሚገድል በሽታ መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት እንዲሁም በ2035 ከቲቢ በሽታ ነፃ የሆነች ሃገር እንድትሆን ለማድረግ በዘመቻ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በተሾመ ኃይሉ