Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል- ርዕሰ መስተደድር ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የክልሉን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ስራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት በክልሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀከቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በተለይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ከማስገንባት አንጻር ክፍተት እንደሚታይ አውስተው በዚህ ላይ አመራሩ የክትትል ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የክልሉ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ከአለም ባንክ በተገኘ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃና ሳኒቴሽን ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በክልሉ ከተገነቡት 17 የህዝብ እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች 8ቱ ተጠናቀው በዛሬው እለት ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

የቀሪዎቹ ግንባታም ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን የገለፁት ሃላፊው በክልሉ ለሚገኙ 409 የደሃ ደሃ አባወራና እማወራዎች የውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ሐረር የቱሪስት መስህብ ስፍራ እንደመሆኗ በክልሉ ከውሃና ጽዳት ጋር የሚከናወኑ ተግባራት አካባቢን ጽዱና ማራኪ በማድረግ ለጎብኚውን እርካታ እንደሚጨምር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.