Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የምርምራ ውጤት ምክረ ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ዝግጁነት አበረታች ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርምራ ውጤት ምክረ ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ዝግጁነት አበረታች መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

ምክትል ኮሚሽነሯ ወይዘሮ ራኬብ መሰለ፥ ኮሚሽኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰብዓዊ መብቶችን ማሳወቅና ማስተማር፣ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና ሕጎች ተፈጻሚነትን መከታተል እንዲሁም የልማት ፕሮግራሞች ሲታቀዱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ማካተታቸውን የማረጋገጥ ስራ ሰርቷል ብለዋል።

በዋናነትም ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ ምክንያት የሚያጋጥሙ የመብት ጥሰቶችን ሲመረምርና ውጤቱን ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።

በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ፤ መጀመሪያ በትግራይ ቀጥሎ በአፋርና አማራ ክልሎች ያጋጠሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ምርመራ መደረጉን አስታውሰዋል።

በኮሚሽኑ በኩል የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ተከትሎ የተሰጠውን ምክረ ሃሳብ ለመተግበር የሚኒስትሮች ግብረ ሀይል ማቋቋሙን በበጎ መልኩ አንስተዋል።

በጥቅሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ በተደረጉ የምርመራ ውጤቶች መሰረት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች አበረታች በሚባል መልኩ እየተተገበሩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የመብት ጥሰት አስመልክቶ 270 ፖሊስ ጣቢያዎች ቅኝት ማድረጉን ጠቁመው በዚህም ከ700 በላይ ያለአግባብ የታሰሩ ግለሰቦች መፈታታቸውንና ሌሎች ማስተካከያዎች መደረጋቸውንም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.