የእሁድ ገበያ የመዲናዋን ነዋሪዎች በመደገፍ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የእሁድ ገበያ ነዋሪዎችን በመደገፍ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ በልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ የእሁድ ገበያ ነው፡፡
አሁን ላይ በከተማዋ ከ50 በላይ የእሁድ ገበያ ስፍራዎች ተቋቁመው ህብረተሰቡ በቀጥታ ከአምራቹ ትኩስ እና ሚዛናዊ በሆነ ዋጋ አስፈላጊ ምርቶችን እንዲገበያይ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
ህብረተሰቡም በሁሉም አካባቢዎች በስፋት እየተገበያየና እየሸመተ ይገኛል፡፡
ይህ ስራ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮና በተደራጀ የአመራር ክትትል አዳዲስ ገበያዎችን በማቋቋም የሚቀጥል ሲሆን፥ በዘላቂነት የአምራቹንና ሸማቹን የግዥ ሰንሰለት በማሳጠር የህገወጦችን አሻጥር በመዝጋት ህብረተሰቡ በሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚደርስበትን ጫና እንደሚቀንስ ታምኖበታል፡፡