Fana: At a Speed of Life!

በወራቤ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትንና የንግድ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ገንዘብ እየተሰባሰበ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰውን ውድመት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙርሰል አማን እንዳሉት ÷የእምነት ተቋማቱን ገንብቶ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰራ ነው።

እስካሁን የተለያዩ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ድርጊቱ የስልጤ ሕዝብ እሴት ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዳወገዘውም አቶ ሙርሰል አውስተዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፥ ድርጊቱ ሃይማኖትን የማይወክል መሆኑን ገልጸው ይህም በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ-እምነቶች መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ርብርብ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፡ ሀይማኖታዊ አስተምህሮዎች ማዕከላቸው የሕዝብ አንድነት መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት አባል ሼህ መሀመድ ሲራጅ በእስልምና እና ክርስትና መካከል ችግር ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደማይሳኩ ጠቁመዋል።

መሰል አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን መከላከልና ማስቆም እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመገንባት ለሌሎች አካባቢዎች ማስተማሪያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.