በበቆጂ ከተማ በተካሄደ የታላቁ ሩጫ ውድድር አትሌት ደጀኔ ሃይሉና አትሌት መሰረት ሂርጳ አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርሲ ዞን በቆጂ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ የታላቁ ሩጫ በ 7 ኪሎሜትር ውድድር በወንዶች አትሌት ደጀኔ ሃይሉ በሴቶች አትሌት መሰረት ሂርጳ አሸንፈዋል።
“ኢትዮጵያ ትሮጣለች” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውድድር በአዋቂዎች 7 ኪሎ ሜትር ሩጫ፣ 15 ኪሎ ሜትር ብስክሌት ውድድርና የህጻናት ሩጫ ተካሂዷል።
በአዋቂ ወንዶች የ7 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ደጀኔ ሃይሉ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ አትሌት ቱሉ አበበ ሁለተኛ፣ አትሌት ብርሃኑ ቱሉ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች 7 ኪሎሜትር ውድድር ደግሞ አትሌት መሰረት ሂርጳራ ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።
ቀነኒ ዲቻ እና ሃዊ ጉደታ እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን መጨረሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት÷ በቆጂ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያስጠሩ ጀግኖችን ያፈራች ከተማ መሆኗን እንዲሁም ታላቁ ሩጫ በቦቆጂ ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በየዓመቱ ለማካሄድ እንደታቀደ ጠቁመዋል።