Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን በመዲናዋ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን የአብርኾት ቤተመጽሐፍት :መስቀል አደባባይ : የማዘጋጃ ቤት ህንፃ እድሳትን ጨምሮ ሌሎችንም አገልግሎት እየሰጡ ያሉና ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስጎብኝተዋል።

እየተጎበኙ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በለውጡ አመራር በአጭር ግዜ የግንባታ ስራቸው ተጠናቆ ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት የተደረጉ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን አመራሩ በዚሁ ልክ በትኩረት ስራዎችን መጀመርና ማጠናቀቅን ባሕል ማድረግ አለበት ተብሏል ።

በጉብኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብልፅግና ሰው ተኮር ነው የምንለው ፤ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉ ፕሮጀክቶችን ነው ተግባራዊ ያደረግነው ብለዋል፡፡

የምገባ ማእከላት አሁን ካሉት ስድስት በተጨማሪ አስተዳደሩ ሌሎች ስድስት በቅርብ ጊዜ ገንብቶ አጠናቆ አስራ ሁለት የምገባ ማእከላት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የትኛውም የኑሮ ጫና ያለበት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችል ማንኛውም የከተማችን ነዋሪ ሄዶ የሚመገብባቸው ይሆናሉም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የከተማው ህዝብ ካስተባበሩት መልካም ህዝብ መሆኑን አዲስ አበባ ማሳያ ናት ያሉ ሲሆን ባለፉት ወራት ከህብረተሰቡ አንድ ቢሊየን ብር በማእድ ማጋራት ሰብስበን ህብረተሰቡ መድረስ የሚችልበት ሲሆን ወደ ሰባት ቢሊየን የሚሆን ደግሞ በድርቁም ለተፈናቀሉም በማዋጣት አብሮነቱን ያረጋገጠበትም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ በከተማና በሀገር አቀፍ ደረጃ ፤በግንባታ ሥራ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችና ሌሎችንም በየደረጃው የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በጥብቅ ክትትል መርቶ በማጠናቀቅ ፤ በተያዘላቸው የግዜ ገደብ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ፤ የተገልጋዩን ሕዝብ እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ መጠቆሙን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.