Fana: At a Speed of Life!

ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ዛሬ ንጋት ላይ መታየቱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ እስፓሻል ኢኒስቲቲዩት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ዛሬ ንጋት መታየቱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ እስፓሻል ኢኒስቲቲዩት አስታውቋል፡፡

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢኒስቲቲዩት እንዲሁም ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር የጨረቃ ግርዶሽ ትዕይንት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ለሠመራና አካባቢ ህብረተሰብ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ እስፓሻል ኢንስቲቲዩት የስፔስ ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ኤፍሬም በሺር እንደገለጹት÷ ክስተቱ መሬት በጸሃይና ጨረቃ መካከል ስትሆን የሚከሰት ነው።

ይህም በተለያዩ ደቡብ አሜሪካና አውሮፓ አገራት እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገራችንም በተለያዩ አካባቢዎች በከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ታይቷል ብለዋል።

በአፋር አካባቢ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ከፊል የጨረቃ ግርዶሹ ሲጀምር በቀላሉ በአይን ሲታይ እንደነበር ገልጸው፥ በሂደት ጭጋጉ እይታ የሚከለክል ቢሆንም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ትዕይንቱን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ተወካይ አቶ ኪሩቤል መንበሩ በበኩላቸው፥ ፕሮግራሙ በአፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ክልሉ መሰል ፕሮግራሞችና ስፔስ ቱሪዝም ያለው ምቹ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ያግዛል ነው ያሉት።

በተለይም ያለው ሜዳማ ሁኔታና ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ በአንጻራዊነት ከጭጋግ የጸዳ ሰማይ እንዲሁም በምሽት ያለው ምቹ አየርና ተያያዥ ሁኔታዎች ለእንደዚህ አይነት ትዕይንቶች አካባቢውን ተመራጭ ያደርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.