ዘንድሮ በድሬዳዋ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ፣ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የደን ልማት ባለስልጣን ገለፀ፡፡
በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም የተመራ ቡድን ዛሬ ረፋድ ድሬዳዋ ተገኝቶ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የተገነባውን ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ጣቢያና ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ እየተካሄዱ የሚገኙ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝቷል፡፡
በዚህ ችግኝ ጣቢያና በሌሎቹ እየተካሄዱ የሚገኙ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ማፍላት ሂደት የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ የሚዘጋጁ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ ከጂቡቲ መንግስት ጋር ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ገልፀው ለአስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው፥ ዘንድሮ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ 2 ሚሊየን የሚጠጉ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡
ከ2 ሚሊየን ውስጥ 150ሺዎቹ ለጂቡቲ የሚላኩና 50 ሺዎቹ ደግሞ ለምስራቅ ተጎራባች ክልሎች በማሰራጨት ምስራቁን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ብለዋል፡፡
እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞች እየተዘጋጁ ሲሆን ÷የቀሩትም በሚፈለገው ጊዜ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ማለታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡