Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ።

የክልሉ የኢንቨስመንት ፎረም “ሃላፊነት የተላበሰ የግብርና ኢንቨስትመንት ለሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ በአሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢኖሩትም በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች አሉ።

ከዚህ በፊት በነበረው ኢፍትሃዊ አሰራር ምክንያት የክልሉ ህዝብ በሃብቱ ላይ የመወሰን ስልጣን እንዳልነበረው አስታውሰው፥ ይህም ህዝቡ የበይ ተመልካች በመሆን በድህነት እንዲቆይ እንዳደረገው ተናግረዋል።

ኪራይ ሰብሳቢነት እና ቢሮክራሲያዊ አሰራርን ጨምሮ የፀጥታ ችግር በዘርፉ እንቅፋት መሆናቸውን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት የተቀናጀ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአርሶ አደሩ ተሞክሮ ከማካፈል ጀምሮ ግብር በአግባቡ በመክፈል የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው፥ በክልሉ ከ2012 ዓም በኋላ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መሻሻሉን አመላክተዋል።

የወሰዱትን መሬት በብድር አስይዘው በመሰወር መንግስትን ከፍተኛ የግብር ገቢ ያሳጡ የአንዳንድ ባለሃብቶችን ጉዳይ ጠቅሰው፥ በዘርፉ አሁንም ማነቆዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

የኢንቨስትመንት ፎረሙ የሚቀጥል ሲሆን፥ ከ300 በላይ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.