Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዘርፈ ብዙ በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታን በይፋ አስጀመሩ፡፡

ዛሬ ክፍለ ከተማው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ለሌላው የከተማው አካባቢዎች ተሞክሮ መሆን የሚችሉ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ ባለባቸው ስድስት ዋና ዋና ዘርፎች የልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጓል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የቤት አቅርቦት፣ የዳቦ አቅርቦት ማሻሻልና ማእድ ማጋራት፣ የከተማ ግብርና፣ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ የአገልግሎት ማሻሻል እና የእሁድ ገበያ ማስፋፋት ይገኙበታል፡፡

የቤት ፕሮጀክቶቹ በተለይም ከነበረው ያረጁ ቤቶች እድሳት በተጨማሪ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ ህብረተሰቡ ከአካባቢውና ማህበራዊ ህይወቱን ከመሰረተበት አካባቢ ሳይፈናቀል በ2 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የዝቅተኛ ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ የሚመጥን ዋጋ ያለው እና ዛሬ የተጀመሩት 4 የጋራ መኖርያ ቤቶች በአጠቃላይ እስከ 200 ቤቶች የሚይዝ ግንባታ ነው፡፡

ይህም ከከተማው እድገት ጋር የሚጣጣም እና ከግል ሴክተሩ ጋር በመተባበር የሚተገበር የG+9 አዲስ አይነት የተገጣጣሚ ቤቶች ነው፡፡

እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች 8 የዳቦ ፋብሪካዎችን በተመሳሳይ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የሚገነቡ ሲሆን፥ 2 የምገባ ማእከላትን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች የሚመገቡባቸው እና 32 የሸገር ዳቦ ማቅረቢያ ቦታዎች በይፋ ግንባታ በይፋ ተጀምረዋል፡፡

በሌላ በኩል በክፍለ ከተማው የከተማ ግብርናን በስፋት በመተግበር በመሃል ከተማ የጓሮ አትክልት በመንገድ ሰዎች ራሳቸውን በምግብ የሚችሉበትን መንገድ በስምንት ሞዴል ቦታዎች የሚተገበር ይሆናል መባሉን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በወቅቱ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፥ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማዋ የሚገባትን እድገት እንድታገኝና በዚህ በእድገትና ለውጥ ውስጥ ደግሞ የዜጎች ህይወት አብሮ የሚቀየርበት ስራዎች ናቸው።

ስለሆነም ነዋሪው እነዚህ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ አብሮ በመስራት በጋራ በመንቀሳቀስ ለስኬቱ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.