በአዲስ አበባ በእንጨት ስራ ድርጅት ውስጥ የተደበቀ ከ3 ሺህ በላይ ጥይት ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ባደረጉት ክትትል በአንድ የእንጨት ስራ ድርጅት ውስጥ ተደብቆ የተቀመጠ ከ3 ሺህ በላይ ጥይት ከእነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ሁለቱ ተቋማት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አዲሱ ገበያ ቀለበት መንገድ አካባቢ በሚገኝ አንድ የእንጨት ስራ ድርጅት ውስጥ ተደብቆ የተቀመጠ ጥይት ስለመኖሩ ከህዝብ የደረሳቸውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ሲከታተሉ ቆይተው፥ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም በህግ አግባብ በድርጅቱ ውስጥ ባደረጉት ብርበራ በ4 ማዳበሪያ ተጠቅልሎ በድብቅ የተቀመጠ 1 ሺህ 98 የብሬን እና 2 ሺህ 162 የክላሽ ጥይት ተይዟል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 2 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሊያስከትል የሚችለውን ሃገራዊ ጉዳት ተገንዝቦ የዚህ ህገ ወጥ ተግባር ተሳታፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየሰጠ ያለውን ጥቆማ እና መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡