በሐረሪ ክልል መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፥ በክልሉ ለሚገኙ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ባላለሙ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት።
በክልሉ ያለውን ውስን መሬት በአግባቡ መጠቀምና ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው÷መሬትን አጥሮ ከማስቀመጥ በተጨማሪ ባለሀብቱ መሬትን ለሌላ አካል ማስተላለፍ እና ከተፈቀደ የኢንቨስትመንት ስራ ውጪ የመስራት አዝማሚያ እንደሚስተዋል አንስተዋል።
በቀጣይ በተሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰራ፣ የስራ እድል ለሚፈጥርና ኢኮኖሚውን ለሚያነቃቃ ባለሀብት እድል ለመስጠትና ለመደገፍ የክልሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
በግንባታ ሂደት ላይ ያሉት በፍጥነት ስራቸውን እንዲያጠናቅቁ እና ምርትና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎችም ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡