ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም ክትትል የሚውል “ቲርዝፓታይድ” የተሰኘ አዲስ መድሃኒት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም ክትትል የሚውል “ቲርዝፓታይድ” የተሰኘ አዲስ መድሃኒት አጸደቀ፡፡
መድሃኒቱ ፈቃዱን ያገኘው ከፌዴራሉ የቁጥጥር ባለሥልጣን ነው ተብሏል፡፡
“ቲርዝፓታይድ” የተሰኘው አዲስ መድሃኒት የ”ዓይነት ሁለት” የስኳር ታማሚዎች በሣምንት አንድ ጊዜ በመርፌ የሚወስዱት ሲሆን ፣ የታማሚዎቹን የደም ስኳር መጠን የሚቆጣጠርና የምግብ አወሳሰዳቸውን እንዲቀንሱ የሚረዳ ተሥፋ ሠጪ መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡
የመድሃኒቱ አምራች ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው የ”ዓይነት ሁለት” የስኳር ታማሚዎች ላይ በሦስት ምዕራፍ ከፍሎ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል።
መድሃኒቱ የታማሚዎቹን ክብደት በመቀነስ እና የስኳር መጠናቸውን በመቀነስ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ አመላክቷል፡፡
የአሜሪካ የስኳር ሕመምተኞች ማኅበር የሣይንስ እና ሕክምና ሃላፊ ዶክተር ሮበርት ጋቤይ ÷ “ቲርዝፓታይድ” የተሰኘው መድሃኒት “ኢንክሬቲን” የተሰኘ የሆርሞን ይዘት ያለውና ጣፊያ ግሉካጎንን እንዲቆጣጠር በማነሳሳት በደም ውስጥ የስኳር መጠን ኢንሱሊን እንዲቀንስ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “ኢንክሬቲን” የስኳር ታማሚዎች የመራብ ስሜት እንዳይሰማቸው እና እንዳይመገቡ የሚያደርግ ሆርሞን መሆኑን ማመላከታቸውን ሄልዝ ላይን ዘግቧል፡፡