የአሸባሪው ህወሓት ጠብ አጫሪ ተግባር የትግራይን ህዝብ አደጋ ላይ የጣለ መሆኑ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ህዝቡን ለጦርነት እየቀሰቀሰ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች በመውጣት ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
አሸባሪው ህወሓት በጠብ አጫሪ ተግባሩ እንደቀጠለና የትግራይን ህዝብ አደጋ ላይ እንደጣለ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገልጸዋል፡፡
በቡድኑ የእብሪት አካሄድ የትግራይ ወጣቶች ወደ እሳት እየተማገዱ መሆናቸውንም ምሁራኑ አመላክተዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ዳግም ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የትግራይን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለመነጠል አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ እየሰሩ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሱራፌል ጌታሁን ይናገራሉ፡፡
ቡድኑ ከትናንት ስህተቱ አለመማሩን በማንሳት ዛሬም በአጥፊ ድርጊት ውስጥ መሆኑንም ምሁሩ አክለዋል፡፡
የህግ ምሁሩ ልጃለም ጋሻው በበኩላቸው፥ ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ቆሜያለሁ ቢልም ከህዝቡ በተቃራኒ መቆሙን በተግባሩ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ቡድኑ የትግራይን ህዝብ አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት ላይ ማተኮሩንም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ህዝብ ህወሓት የህልውናው አደጋ መሆኑን በመገንዘብ ለጥፋት ድርጊቱ መተባበር እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።
የህወሓት ጥፋት እንዳይደገም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ሀገሩን ከጥፋት እንዲታደግ ምሁሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ