Fana: At a Speed of Life!

ህጋዊ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ምክክር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በምክክሩ ላይ አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከንግድ ቢሮዎች፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን እንዲሁም ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች የተውጣጡ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፥ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ የተስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ያሳለፍነው ሚያዚያ ወር የትንሳኤ በዓል እና 1443ኛው የኢድ በዓል የተከበሩበት ወቅት በመሆኑ በእነዚህ በዓላት ምክንያት ነዳጅ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ ባለመጫኑ በተፈጠረ ክፍተት ጊዜያዊ የነዳጅ እጥረት በመከሰቱ በየማደያዎቹ የተሽከርካሪዎች ሰልፍ መስተዋሉ ተገልጿል፡፡

የአቅርቦት ውስንነት፣ የቁጥጥር ስርዓቱ ድክመት፣ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ባለው የነዳጅ ማጓጓዝ ሂደት የነዳጅ ቅሸባና የአሽከርካሪዎች በየቦታው ለረጅም ሠዓታት መቆም እንዲሁም መንግስት ከፈቀደው የግብይት ቦታና ዋጋ ውጪ የዋጋ ጭማሪ አድርጎ በህገ-ወጥ መልኩ የመሸጥ ፍላጎት የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭቱን እየፈተኑት ያሉ ችግሮች መሆናቸውም ተብራርቷል፡፡

ችግሮቹን በመፍታት ምርቱን ለተጠቃሚው ለማድረስ አሰራርን ከማስተካከል ጀምሮ መንግስት ከዘረጋው የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ሂደት ውጭ በሚፈጽሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ተብሏል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ጥናቶችን በማካሄድ በነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭትና ቁጥጥር ሂደት ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከስምምነት በላይ መደረሱንም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.