Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው-የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷በአረንጓዴ አሻራ መርሃሐ ግብሩ ከሚተከለው ችግኝ 60 በመቶ የሚሆኑት ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እና ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ ችግኞች እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመትከል ኢኮኖሚውን መደገፍ እና ለአረንጓዴ አሻራውም አስተዋፅኦ የማድረግ ግብ ተይዞም እተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

5 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞች ዝግጁ መደረጋቸውን የክልሎች ሪፖርት እንደሚያሳይ ያነሱት አቶ ኡመር÷ የቅድመ ዝግጀት ስራዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉበት ደረጃ እየታየ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለተከላ ዝግጁ የተደረጉ ችግኞችን ጨምሮ ለመትከያ ቦታ የተደረጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ያሉበት ደረጃ በባለሙያዎች ምልከታ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ ዝርዝር መርሐ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ባለፉት 3 ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ሲተገበር የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ጥሩ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ዳሰሳም ባለፈው ዓመት የተተከለው ችግኝ የጽድቀት መጠን 80 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.