Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በመኸር እርሻ 143 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 143 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ቀደም ብሎ በመኸር የእርሻ ወቅት 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታስቦ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ መገኘቱን ተናግረዋል ።
 
በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩልም 240 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘርን ለማቅረብ ታቅዶ 212 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መቅረቡንና የመጀመሪያው የሰብል ሽፋን ከሚያገኘው የበቆሎ ምርት 80 ሺህ ኩንታሉ ምርጥ ዘር ወደ አርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቁመዋል ።
 
የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ችግሮች አሉብን ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው÷ ይህንም በተፈጥሮ ማዳበሪያ እና በፈሳሽ ማዳበሪያ ለመተካት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ክልሉ እንደ አገር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የገጠመውን የማዳበሪያ እጥረት ችግር ለመፍታት 70 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት አቅዶ ከ36 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ዝግጁ በመሆኑ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ ነው ተብሏል ፡፡
 
በሌላ በኩል የፈሳሽ ማደበሪያ አቅራቢዎችን 11 ነጥብ 3 ሚሊየን ሊትር የፈሳሽ ማዳበሪያ እንዲያቀርቡ ተጠይቆ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው÷ መሰል የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግዢ መፈፀም የማይችሉ አርሶ አደሮችም አገልግሎቱን በብድር ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
የማዳበሪያ አቅርቦቱ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑንያነሱት ምክትል ሃላፊው ÷ችግሮችን በምንችለው አቅም ሁሉ ተቋቁመን በመስራት የዘንድሮው የመኸር ምርት በቀጣዩ ዓመት ላይ አሉታዊ ሚና እንዳያሳርፍ ለማድረግ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
 
በጸጋዬ ወንድወሰን
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.