Fana: At a Speed of Life!

ሰኔ 24 ለሚጀመረው ሁለኛው ዙር የኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት ስኬት ሁሉም ባለድርሻ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለኛው ዙር የኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት የኢትዮጵያን ገፅታ ይበልጥ ለማስተዋወቅ በሚያስችል ደረጃ እንዲዘጋጅ ሁሉም ባለድርሻ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ከኢድ እስከ ኢድ ክብረ በአል የመርሃ ግብሮች አፈፃፀም፣ የእስካሁን ስራዎች እና ቀጣይ ተግባራትን የገመገመ ውይይት ብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ትላንት በበይነ መረብ አከናውኗል።

በውይይቱ እስካሁን ሲደረግ የነበረው የመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር በአብዛኛው በታቀደው መሰረት እየተፈፀመ መሆኑ ተመልክቷል።

የብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሃገር ውስጥ ተቋማት መካከል እንዲሁም ከሚሲዮኖች ጋር በጥሩ ቅንጅት በመስራት የመጀመሪያውን ዙር ከኢድ እስከ ኢድ ክብረ በአል በስኬት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የተገኘው ተሞክሮም የሁለተኛው ዙር ስራዎችን በላቀ ሁኔታ ለማከናወን እገዛ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የብሄራዊ ኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፥ በመጀመሪያው ዙር የኢድ እስከ ኢድ አከባበር ሃይማኖታዊ ይዘቱን የጠበቀ፣ ህዝብን በነቂስ ያሳተፈ እና የሃገርን ገፅታ ያስተዋወቀ እንደነበር ተናግረዋል።

ከመርሃ ግብሮቹ አንዱ የሆነውን ታላቁ የኢድ ሶላትን ለማወክ የተሞከረው እንቅስቃሴ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር መቻሉን በማስታወስ ለዚህም የፀጥታ አካላትን አመስግነዋል።

በቀጣይ መርሃ ግብር የተያዙ ታላላቅ ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ መርሃ ግብሮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ሁለተኛው ዙር ከኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት ሰኔ 24 ቀን 2014ዓ.ም እንደሚጀምር በውይይቱ የተገለፀ ሲሆን፥ ህዝብን አሳታፊ የሆኑ መርሃግብሮች መታቀዳቸውም ታውቋል።

አንዳንድ ተቋማት ላይ በመጀመሪያው ዙር የታየው ሃላፊነትን በሚጠበቀው መጠን ያለመወጣት ክፍተት በሁለኛው ዙር እንዲታረም ተጠይቋል።

ሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር በተሻለ የተቋማት ቅንጅት እና ቅድመ ዝግጅት የሃገሪቱን ገፅታ ይበልጥ ማጉላት በሚያስችል መልኩ ለመፈፀም እንዲሰራም ነው የኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.