ጫናዎችን በህዝብ ጽናት ፣ በዳያስፖራው ተሳትፎና በዲፕሎማሲ ተቋቁመን የከፋ ችግር ሳይደርስ ቀጥለናል – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ የሃገር ሉዓላዊነት እንዲከበር፣ በጋራ ጥቅምና እኩልነት የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት የተመሰረተ ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በማካሄድ እና የገጽታ ግንባታ ስራዎች መከናወኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲጠበቅ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም ሁለንተናዊ የዳያስፖራ ተሳትፎን ማጠናከር የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ባለፉት 9 ወራት የተከናወኑ ዐብይ ተግባራትን አቅርበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት ፥ ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎች ተጋርጠውባት ስትፈተን እንደቆየች ጠቅሰው፥ ፈተናውን ለመሻገር ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዲፕሎማሲውን በመደገፍ ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉበት ዓመት እንደሆነ አንስተዋል።
በዚህ ወቅትም አንድነታችን ካልጠበቀ፣ ኢኮኖሚያችን ካልጠነከረ፣ ሰላማችን ካልሰፈነ የቱንም ያህል ጥረት ቢደረግ የውስጥ ሁኔታችን በዲፕሎማሲው ላይ ጫና ማሳደሩ እሙን ነው ብለዋል፡፡
ውስጣዊ ችግራችን በዲፕሎማሲያችን ከፈጠረው ፈተና ባሻገር የኢትዮጵያን ሰላም፣ እድገትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት የማይፈልጉ ሃይሎች ላነገቡት እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲረዳቸው የሚያሳድሩት ተመጋጋቢ ጫና እና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚጠቀሱ ፈተናዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ጫናዎችን በኢትዮጵያ ህዝብ ጽናት እና ጥረት፣ በውጭ በሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ፣ በቁርጥ ቀን ወዳጆችና በዲፕሎማሲ በመቋቋም የከፋ ችግር ሳይደርስና መስመራችንን ሳንለቅ ቀጥለናል ነው ያሉት፤ ለዚህም ለመላው ህዝብና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጫናዎቹ በተወሰነ ደረጃ የመለዘብ ምልክት ቢያሳዩም በተለያየ መልኩ ቀጥለዋል ያሉት አቆ ደመቀ መኮንን፥ ውስጣዊ አንድነታችንን በመጠበቅ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በማስገንዘብና በማለዘብ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍኖተ ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጀንዳ መቀረጹንም አስረድተዋል።
ዓላማውም ሚኒስቴሩ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የገጽታ ግንባታ፣ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና የዳያስፖራ ልማትና ተሳትፎ ግቦችን ለማሳካት ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ያጋጠሙትን መሰናክሎች ተቋቁሞ ማለፍ እንዲችል ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የተካሄዱ የለውጥ ፓኬጅ አፈጻጸሞች ጥንካሬና ክፍተቶቻቸውን ምን እንደሚመስሉ ለይቶ የማቅረብ፣ ተቋሙ ተልዕኮውን ከማሳካት አንጻር ባለፉት ዓመታት ምን አከናውኗል፣ አሁንስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ወደፊትስ የት መድረስ ይፈልጋል የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባቀረቡት ሪፖርት ስለኢትዮጵያ እና ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፥ ሀገራቱ በሚጋሩት ወሰን ለረጅም ዘመናት የቆየ የይገባኛል ጥያቄ መኖሩን አንስተዋል፡፡
ይሄን ችግር ለመፍታትም የተዘረጋ ስርዓት መኖሩን አንስተው ፥ ሆኖም ትኩረቱ ወደሰሜኑ ጦርነት ሲዞር ሱዳን ዘላቂው መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ብለን አክብረነው የቆየነውን ስምምነት በመጣስ መውረሯን ገልጸዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ህዝብ እጅጉን ያስቆጣ እና የአካባቢው ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ወረራውም ከፍተኛ መፈናቀል፣ ሃብት ንብረትን ያወደመ እና ብዙ ጫናዎችን ያደረሰ ነውም ብለዋል፡፡
ሱዳን ያደረገችው ወረራ ጂኦግራፊውንና ዲሞግራፊውን ለመቀየር የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እያካሄዱ እንደሆነ ያነሱት አቶ ደመቀ ፥ ይህ ተገቢ እንዳልሆነ በማሳወቅ በኩል ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ የዓለም አገራት እንዲያውቁት ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይሄ ወረራ አደገኛ ውጤት የሚያስከትል እንደሆነ ጠቅሰው ፥ ኢትዮጵያ ለሰላም በሯን ከፍታ እየጠበቀች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ ኢትዮጵያ ለሰላም እያሳየች ያለችውን ጥረት ማበረታታት ቢኖርም ሱዳን እያደረገችው ያለውን ወረራ በግልጽ በማውገዝ በኩል ከፍተኛ ክፍተት እንደሚታይም ነው የገለጹት፡፡
የአሸባሪው ህወሓት ሃይሎች በስደተኛ ስም በሱዳን በኩል በተለያየ ጊዜ እያደረሱ ያሉት ጥቃት እንዳለ አንስተው ፥ ይህም ሊታረም እንደሚገባ በይፋ አሳውቀናል ሲሉም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡
ይህ ችግር በሰላም እንዲፈታ ማድረግ የሚቻለውን በሙሉ ማድረግ እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን ፥ በየትኛውም መመዘኛ ግን የኢትዮጵያ ግዛት ይመለሳል ብለዋል፡፡
በመሰረት አወቀ