በጥብቅ ደንነት በዩኔስኮ የተመዘገበው የማጃንግ ጥብቅ ደን እየወደመ መሆኑ ተነገረ
የጎደሬ ወረዳ የካቢኔ አባላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በህገ ወጥ ግለሰቦች የተጨፈጨፈውን የማጃንግ ደን ባዮስፌር ሪዘርቭ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የጎደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይስሐቅ አብርሃም ÷ አንዳንድ ጊዜያዊ ጥቅም ፈላጊ ህገ ወጦች እያደረሱ ባሉት የደን ጭፍጨፋ ተፈጥሯዊ ደኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ይህን ለመከላከል በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህገወጥ ደን ጨፍጫፊዎች ምክንያት ከ300 እስከ 400 ዓመት የሆናቸውን እድሜ ጠገብ ዛፎችን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ጭፍጨፋ በማካሄድ የደኑ ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልፀዋል።
በመሆኑም በፍጥነት እየተካሄደ የሚገኘውን ወረራና የደን ጭፍጨፋ ለመከላከል ወራሪዎቹን የመለየት ፣ ከጥብቅ ደኑ ይዞታ የማስወጣትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የጎደሬ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ካድሬ አበበ በበኩላቸው÷ ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚገባ ተናግረው ለዚህም ህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በማጃንግ ባዮስፌር ሪዘርቭ ውስጥ 550 የሚደርሱ የእፅዋት ፣ከ180 በላይ የአዕዋፍ ፣ 33 የአጥቢ እና 20 ተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኙበታል።
በአደም አሊ