Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የመሳሪያ ሥርጭት እና ቁጥጥር አተገባበሯን እንድትፈትሽ ቻይና ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ መሣሪያ በታጠቁ ሁከት ፈጣሪዎች በዜጎቿ ላይ የሚፈጽሙትን የሽብር ተግባር እንድትቆጣጠርና እርምጃ እንድትወስድ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ጠየቁ፡፡

ቃል አቀባዩ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ከመሣሪያ ጋር የተገናኙ ሁከትና የሽብር ተግባራት በአሜሪካ እየተባባሱ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በዚህ ዓመት በአሜሪካ በመሣሪያ በተፈጸሙ የሽብር ተግባራት 50 ሺህ 569 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አንስተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ደግሞ 20 ሺህ 726 አሜሪካውያን ከመሣሪያ ጋር በተያያዘ ብጥብጥ እና ሁከት ሕይወታቸውን አጥተዋል ነው ያሉት።

ቃል አቀባዩ የችግሩን አሳሳቢነት በማነጻጸር ሲገልጹም በዚህ ዓመት 5 ወራት ብቻ ከመሣሪያ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጡ አሜሪካውያን ዜጎች ቁጥር ካለፈው ዓመት 12 ወራት አንጻር ሲታይ ወደ ሶስት እጥፍ መጠጋቱን ጠቅሰዋል።

በአሜሪካ ዜጎች መሣሪያ በቀላሉ የሚገዙበት ሁኔታ እንዳለም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡

ዣኦ ሊጂያን የአብዛኞቹ አሜሪካውያን ሕይወት እየተቀጠፈ ያለው ከዘር አድልኦ ፣ ጽንፈኝነት እና የዘር ጥላቻ ጋር በተያያዘ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በፈረንጆቹ 2020 መሣሪያ የገዙ የአፍሪካ-አሜሪካውያን ቁጥር በመቶኛ በ58 ነጥብ 2 ጭማሪ ማሳየቱንና 43 በመቶ የሚሆኑ የእስያ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያንም በተመሳሳይ ዓመት መሣሪያ እንደገዙ ነው የተናገሩት፡፡

መሣሪያ የገዙት አሜሪካውያን መሣሪያ የሚታጠቁት በአሜሪካ ከሰፈነው የዘር አድልዖ ጋር በተያያዘ የደኅንነት ስሜት ስለማይሰማቸው እና ራሳቸውን ለመከላከል መሆኑን ቃል አቀባዩ አመላክተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 ከትራፊክ ህግ መጣስ እና ከህግ አካላት ጋር በተፈጠረ እሰጥ-አገባ ከ500 በላይ አሜሪካውያን በመሣሪያ ተመተው ለህልፈትና ጉዳት እንደተዳረጉም አመላክተዋል።

አሜሪካ የዓለማችንን 4 ነጥብ 2 በመቶ ሕዝብ የምትይዝ ሀገር እንደሆነች እና 46 በመቶ ያህሉ አሜሪካውያን መሣሪያ መታጠቃቸው ለዜጎች ደኅንነት አሳሳቢ እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም አሜሪካ እየተባባሰ ለመጣው ዘር ተኮር ጽንፈኝነት እና ጥላቻ እልባት እንድታበጅለት እና የዜጎቿን ደኅንነት ለማረጋገጥም ጠንካራ የመሣሪያ ቁጥጥር ደንብ ልታወጣ እና ልትተገብር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአሜሪካ ከመሣሪያ ጋር የተያያዘ የሽብር ተግባር እንደ ኮቪድ 19 ሁሉ አሳሳቢ ወረርሽኝ ሆኗል ማለታቸውን ሺንዋ በዘገባው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.